
አቶ አለምአንተ አግደው ወንድሜነህ የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት የቦርድ ሰብሳቢ
የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት የቦርድ ሰብሳቢ መልዕክት የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የስልጠና ስርዓትት ለጠንካራ የዳኝነትና የፍትህ ስርዓት አንዱ ምሰሶ ነው። በሀገራችን ብሎም በክልላችን የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ሥልጠና ሥርዓት የመዘርጋት እና የተቋም ግንባታ ጉዳይ ረጅም የሚባል ጊዜን የቆየ ባይሆንም ሥርዓቱን በመቅረፅ እና ተቋም እንደገና በማደራጀት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህና የሕግ ኢንስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 299/2017 ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ ሆኖ በክልላችን ለዳኞች፣ ለዐቃቤያነ-ሕግና ሌሎች የፍትሕ አካላት ስልጠና የሚሰጥ እንዲሁም የሕግ ጥናትና ምርመምር የሚያካሂድ የክልሉ የፍትሕና የሕግ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለማገልገል የተቋም ግንባታ የሪፎርም ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን ይህን ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት ቀጣይነት ያላቸው የሪፎርም ሥራዎችን ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ሥራውን በብቃት ማከናዎን እንዲያስችለውም የሕግ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት አቻ ተቋማት ጋር በአጋርነት የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓትን ለማጠናከር ይሰራል፡፡ ዳኛ ለመሆን የዳኝነት ሹመት ብቻ በቂ አይደለም፤ ለዕድሜ ልክ ትምህርትና ሥልጠና ቁርጠኝነት አስፈላጊ ነው። ለሌሎች ባለሙያዎችም ተመሳሳይ ነው፡፡ በህብረተሰቡ እና በሕግ ሥርዓታችን ውስጥ ነገሮች ምን ያህል በፍጥነት እንደሚለወጡ ከግምት በማስገባት ዳኞችና የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ለሥራቸው አስፈላጊ እና አዳጊ የሆኑ የዕውቀት፣ የክህሎትና የማህበራዊ ዐውድ አረዳድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የአብክመ የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ስልጠና ሥርዓት ሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡- ዕውቀት፣ ክህሎት እና የማህበራዊ ዐውድ ግንዛቤ ናቸው፡፡ የኢንስቲትዩቱ የሥልጠና ሥርዓት የፍርድ ቤቶችን እና ለሎች የፍትሕ አካላትን ተቋማዊ ነፃነት ጠብቆ አቅምን ለመገንባት የሚተጋ ሲሆን በተለይም የፍርድ ቤቶችን እና የዳኞችን ተቋማዊ እና ሙያዊ ነፃነት የማረጋገጥ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱን እንደገና በአዋጅ መቋቋም ተከትሎ ተቋሙ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ ከመሆኑም በላይ አሁን ላይ የኢንስቲትዩቱን የበላይ አመራር በማስተባበር በቦርድ ሰብሳቢነት እየሰራሁ ሲሆን የኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ እንዲሳካ በምንሰጠው አመራር ደስተኛ ነኝ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ኢንስቲትዩቱ በሕግ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት እንዲወጣ በክልላችን ካሉ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ሠራተኞች እና አመራሮች በተጨማሪ ሌሎች በዘርፉ እየሰራችሁ ያላችሁ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆናችሁ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት እና አመራሮች ከኢንስቲትዩቱ ጋር በትብብር እና በመደጋገፍ በመስራት ለጠንካራ የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓት ግንባታ የበኩላችሁን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ጥሪ ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ አለምአንተ አግደው ወንድሜነህ የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት የቦርድ ሰብሳቢ
