የተቋሙ አመሰራረት

ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘግይታም ቢሆን መተግበር የጀመረችውን እና በ1994 ዓ.ም የተካሄደውን ዝርዝር ጥናት መነሻ በማድረግ የወቅቱ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራምን ቀርፆ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን የሚቀርፍ ሪፎርም ለማካሄድ ወደ ሥራ በገባበት ወቅት ለፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ትግበራ ጅማሮ መነሻ ናቸው ካላቸው የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓቱ ችግሮች መካከል በቂና ብቃት ያላቸው ዳኞችና ዐቃቤያነ-ሕግ አለመኖር፤ ለዳኞች የቅድመ-ሥራም ሆነ የሥራ ላይ ሥልጠና የማይሰጥ መሆኑ፤ ከዐቃቤያነ-ሕግ እና ዳኞች ምልመላና ሥልጠና ሥርዓት ጋር ያሉ ችግሮች፣ የባለሙያ እጥረት፣ ብቃት ያላቸው የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋማት እጥረት፣ የሕግ ሥልጠናና ፖሊሲ ሥርዓት አለመኖሩ እና የዳኞች፣ የዐቃቤያነ-ሕግና ፖሊስ ሥልጠና ተቋምና ሥርዓት አለመኖር፤  ከጥናትና ምርምር ሥራዎች ተደራሽነትና ጥራት ጋር የተያያዙ ሰፋፊ ችግሮች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ የዳኞችና የፍትሕ አካላት ሥልጠናና የሕግ ምርምር ተቋማት በፌደራል እና በክልሎች በአዲስ መልክ እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡

የአብክመ የፍትሕ ባለሙያዎችና ማሰልጠኛ ተቋምም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስተባባሪነት ክልሉ ከመለመላቸው ከ700 በላይ የቅድመ-ሥራ ሰልጣኞች ባለፈ ከአጎራባቾቹ የቤንሻንጉል ጉምዝ እና የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተመልምለው የመጡለትን ሰልጣኞች ጭምር በመቀበል ወረታ ከተማ በሚገኘው የግብርና ኮሌጅ የካቲት 1 ቀን 1999 ዓ.ም ሥራውን አሀዱ ብሎ ጀምሯል፡፡ ተቋሙ በመቀጠል በ2003 ዓ.ም በክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 74/2003 መሰረት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትሕ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ እና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት የሚል ስያሜ በመያዝ ተጠሪነቱ ለክልሉ ፍትሕ ቢሮ ሆኖ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ከዚህ በመቀጠል በ2017 ዓ.ም ደግሞ በክልሉ ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 299/2017 የአብክመ የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት በሚል ስያሜ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ እንዲሆን ተደርጎ ተቋቁሟል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ሥራውን ከጀመረበት 1999 ዓ.ም ጀምሮ ለአዲስ የሕግ ምሩቃን የቅድመ-ሥራ ስልጠናዎችን፣ የቅድመ-ሥራ ስልጠና ከመጀመሩ በፊት የዳኝነት እና የዐቃቤ-ሕግነት ሙያን ለተቀላቀሉ ዳኞችና ዐቃቤያነ-ሕግ የመካከለኛ ጊዜ የሥራ ላይ ስልጠናዎችን፣ ከዳኝነትና ፍትሕ ተቋማት ባለሙያዎች ባለፈ ለፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማነት ድርሻ ያላቸው ተቋማት ባለሙያዎችን ጨምሮ የአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሕግ ጥናትና ምርምር ሥራውን ከጀመረበት 2006 ዓ.ም ጀምሮ በዋናነት በክልሉ የፍትሕ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና የሕግ እና የአሰራር ክፍተቶች ላይ መሰረት ያደረጉ የሕግ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ ዓመታዊ የሕግ ምርምር መፅሔት በማሳተምም ለክልሉ ፍትሕ ሥርዓት ውጤታማነት የድርሻውን እያበረከተ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

Establishment Proclamation

 

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩትን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ
ሙሉውን ለማግኘት ሊንኩን ይጫሉ

299.17 Institute of justice and law proclamation.pdf

Scroll to Top