
ዶ/ር ደሴ ጥላሁን አያሌው
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መልዕክት
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህና የሕግ ኢንስቲትዩት ተጠሪነቱ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆኖ በክልሉ ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 299/2017 ዓ.ም እንደገና የተደራጀ የክልሉ መንግስት የፍትህና የህግ የልህቀት ማዕከል ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የክልሉን የዳኝነትና የፍትህ አካላት ቀልጣፋ፤ ውጤታማ፤ ተደራሽ፤ ገለልተኛ እና የህዝብ አመኔታን ያረፉና እርካታን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ፤ የዳኝነትና የፍትህ ዘርፉን አመራሮችና ባለሙያዎች በዕውቀት፤ በክህሎት፤ እና በሥነ-ምግባር በማነፅ ዘርፉ ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት እና ሥነ-ምግባር ባላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲገነባ በማስቻል፤ በጥናትና ምርምር ውጤት ላይ የተመሰረተ፤ የተተነተነ የፍትህ አስተዳደር ሥርዓት መረጃ ማዕከል በማበልፀግ፤ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የሥልጠናና የጥናትና ምርምር የልህቀት ማዕከል ሆኖ የማገልገል ተልዕኮ ያለው ነው፡፡
ኢንስቲትዩታችን የክልላችን የፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላት የትራንስፎርሜሽን አመራር አዲስ ዕሳቤ ውልድ ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በዳኝነትና በፍትህ አካላት ሥልጠናና የህግ ምርምር አገልግሎት ሰፋፊ ሥራዎችን የሰራ ሲሆን በቅድመ ሥራ ሥልጠና በ17 ዙሮች ከ4500 በላይ ዳኞችና ዐቃቤያነ-ህግ ሰልጥነው የዳኝነት እና የፍትህ ሥርዓቱን ተቀላቅለዋል፤ በሥራ ላይ ሥልጠና ደግሞ ከ1300 በላይ ዳኞችና ዐቃቤያነ-ህግ የመካከለኛ ጊዜ የሥራ ላይ ሥልጠና ተከታትለው ወደ ተቋሞቻቸው የተመለሱ ሲሆን በጥናትና ምርምር ዘርፍ ደግሞ በ9 ቮልዩሞች ከ60 በላይ ርዕሠ-ጉዳዮች ለህትመት በቅተዋል፡፡ ሆኖም እንደ ተቋም መሰረታዊ እና መዋቅራዊ የሚባሉ የተቋም ግንባታ ተግዳሮቶች ስለነበሩብን ኢንስቲትዩቱን በተለወጠ ዕሳቤ እና አዳዲስ ተልዕኮዎች እንደገና በማደራጀት ለፍትህና ለህግ የልህቀት ማዕከልነት እየተጋን እንገኛለን፡፡
ኢንስቲትዩታችን እንደገና የተደራጀበትን አዋጅ ቁጥር 299/2017 ዓ.ም እና የዳኝነትና የፍትህ ዘርፉን ተልዕኮ እንዲሁም የክልሉን መንግስት የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ፍኖተ-ካርታ መነሻ በማድረግ አምስት የትኩረት መስኮችን ቀርፆ እየሰራ ይገኛል፡- ተቋማዊ ፋሲሊቲና የመፈፀም አቅም ግንባታ፤ የዳኝነትና የፍትህ አካላት ሥልጠና፤ የፍትህና የህግ ጥናትና ምርምር፤ ሥትራቴጂክ አጋርነት፤ ኮሚዩኒኬሽንና የገቢ አቅም ግንባታ እና የፍትህና የህግ መረጃ ማበልፀግና ዲጂታላይዜሽን ናቸው፡፡
ኢንስቲትዩታችን ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት ከፍርድ ቤቶች፤ ከፍትህ ተቋማት፤ ከሕግ ትምህርት ቤቶች፤ ከአገር ውስጥና ከውጪ አገራት አቻ ተቋማት ጋር በቅርበት የሚሰራ ሲሆን የዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቱን ለማጠናከር ከሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት ጋር በትብብር ይሰራል፡፡ የክልሉ መንግስት ብቸኛ የዳኝነት እና የፍትህ አካላት የሥልጠናና የህግ ምርምር ማዕከል በመሆናችን ተልዕኳችን መሰረታዊና ግዙፍ መሆኑን በመገንዘብ ተግተን እንሠራለን፡፡
በፍትህና የህግ ሥልጠና ዘርፍ ከህግ ትምህርት ቤቶች በህግ በመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃንን ተቀብሎ በቅድመ ሥራ ሥልጠና በማብቃት ወደ ዳኝነትና ፍትህ ሥርዓቱ እንዲቀላቀሉ የምንሰራ ሲሆን፤ የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን፤ በባለድርሻ አካላት ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ልዩ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ በህግ ጥናትና ምርምር ዘርፍ የክልሉን አጠቃላይ የህግና የፍትህ ሥርዓት የሚያግዙ ምርምሮችን በማካሄድ ምክረ-ሃሳቦችን እናቀርባለን፡፡ የዳኝነትና የፍትህ አካላት ሥልጠናና ምርምር ሥራችን ዓለም-አቀፋዊነትን የዋጀ እና በዲጂታላይዜሽን ተደግፎ ዘመናዊነትን እንዲላበስ ለማድረግ በዘርፉ አጋርነትን በማጠናከር ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር የምንሰራ ሲሆን በዘርፉ ካሉ አደረጃጀቶች ጋር እስከ አባልነት በደረሰ ተሳትፎ እንሰራለን፡፡
አጠቃላይ የኢንስቲትዩታችን ርዕይ በ2022 ዓ.ም ለፍትህና የህግ የልህቀት ማዕከልነት የሚያበቁ የተቋም ግንባታ ሥርዓት መሰረቶች ዕውን ሆነው ማየት ሲሆን በ2027 ዓ.ም ደግሞ ቴክኖሎጂ መር ውጤታማ የፍትህና የህግ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ማየት ነው፡፡ በ2042 ዓ.ም ደግሞ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ተጠቃሽ የሆነ የፍትህና የህግ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ማየት ነው፡፡ ለዚህ የርዕይ ጉዞ የምንመራባቸውን እሴቶች ቀርፀናል፡- ለፍትህና ለህግ የልህቀት ማዕከልነት መትጋት፤ ተቋማዊ ነፃነት፤ ገለልተኝነትና ተጠያቂነትሙያዊ ብቃትና ፈጠራ፤ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት፤ ሥትራቴጂካዊ አጋርነትና ቅንጅታዊ አሠራር፤ አሳታፊ አመራር ሰጪነትና ታማኝነት፤ ሥነ-ምግባራዊ ምሳሌነትና የለውጥ አስቀጣይነት ናቸው፡፡
በክልላችን ነፃ፤ ገለልተኛና ብቃት ያለው የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ርብርብ ተቋማዊ አድርጎ ለማስቀጠል ሥለምንሠራ ኩራት ይሰማናል፡፡ ጠንካራ የፍትህና የህግ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር በተቋማዊ አቅምነት ሥለምንሰራ ኃላፊነታችን ከፍ ያለ ነው፡፡ አጠቃላይ የኢንስቲትዩታችን አመራርና ሠራተኛ ለተቋማችን ተልዕኮ ስኬት በትጋት ይሰራል፡፡ ለወሳኝ ባለድርሻ አካላትም አብረን ጠንክረን እንድንሰራ የአጋርነት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ለፍትህና ለህግ የልህቀት ማዕከልነት እንተጋለን !
ዶ/ር ደሴ ጥላሁን አያሌው
ዋና ዳይሬክተር
