የአብክመ የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት የተቋማት አጋርነት አካል የሆነው የጥናትና ምርምር ሥነ-ዘዴ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተጠናቀቀ

የአብክመ የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት የተቋማት አጋርነት አካል የሆነው የጥናትና ምርምር ሥነ-ዘዴ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተጠናቀቀ

የአብክመ የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት በህግና የፍትህ ሥልጠና፤ የጥናትና ምርምር እና የመረጃ ማዕከልነት የልህቀት ማዕከል (Justice and Law Center of Excellence) እንዲሆን በኢንስቲትዩቱ እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት መፈፀም እንዲችል በዘርፉ ተቀራራቢ ተልዕኮ ካላቸው የክልሉ እና የፌደራል ተቋማት ጋር የጋራ መግባቢያ ስምምነት በመፈራረም እና አጋርነት በመፍጠር እየሰራ ሲሆን ከአብክመ ስቴት ዩንቨርስቲ ጋር በተፈራረው የጋራ መግባቢያ መሰረት ለኢንስቲትዩቱ አሰልጣኞችና ተመራማሪዎች የምርምር ሥነ-ዘዴ ላይ (Advanced Legal Research Methodology for ANRS Justice and Law Institute) የሶስት ቀናት ስልጠና በማዘጋጀት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ የስቴት ዩንቨርስቲው የምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቹቹ አለባቸው፤ የስቴት ዩንቨርስቲው ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር ሃይሌ ደረጀ፤ እና የባህር ዳር ዩንቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር ነጋ እውነቴ በአሰልጣኝነት ሥልጠናውን በአደገ ሁኔታ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

ስልጠናው በህግ ዘርፍ በስፋት የሚተገበረውን የዶክትሪናል የምርምር ዘዴ ከኢምፔሪካል የምርምር ዘዴ ጋር በማጣመር የኢንስቲትዩቱን ችግር ፈቺ የምርምር ተልዕኮ (Action Research Mandate) አሁን ላይ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ በመጣው የቅይጥ የምርምር ዘዴ (Mixed Legal Research Methods) ታግዞ ይበልጥ ሳይንሳዊ እና ተዓማኒነት ያለው የምርምር ምክረ-ሃሳብ ለማቅረብ የሚያግዝ አቅም የፈጠረ ነው፡፡ በመሆኑም፤ በቀጣይም የተቋማትን የጋራ አቅም በመጠቀም የጋራ ተልዕኮዎችን በውጤታማነት ስራዎችን ለመስራት፤ በምርምሩ ዘርፍ ሃብት የሚጠይቁ ቴክኖሎጂን እና የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥነ-ዘዴ ሶፍትዌሮችን ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ መንግስት የምርምር ተቋማት የጋራ ኮንሶርቲየም ጭምር እየፈጠሩ በጋራ መስራት ያለባቸው መሆኑን በስልጠናው ተጠቁሟል፡፡

በሥልጠናው የስቴት ዩንቨርስቲው አሰልጣኞችና ተመራማሪዎች ከኢንስቲትዩቱ አሰልጣኝና ተመራማሪዎች ጋር በጋራ ሆነው የተሰጠ ሲሆን ልምዶችን ለማካፈል እና እርስ በእርስ ለመማማር ዕድል የሰጠ ሲሆን ሥልጠናውን የሰጡት አሰልጣኞች በበኩላቸው ሃሳባቸውን ያጋሩ ሲሆን ቹቹ አለባቸው (ዶ/ር) እና ኃይሌ ደረጀ ዶ/ር እንደገለጽት፣ ስልጠናው በዚህ አጭር ጊዜ ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ ተነስቶ ይህንን የመሰለ መረዳት ተይዞ የተሰጠው ምላሽ ከስኬትም በላይ በጣም ጥሩ ግንዛቤ ተጨብጧል፤ ካሉ በኃላ ወደ ፊት ቀጣይነት ባለው መልኩ ተከታታይ ድጋፍ በማድረግ በጋራ መስራት እንደሚችሉ አስረድተዋል። ነጋ እውነቴ (ዶ/ር ) በበኩላቸው የነበረው ተሳትፎ በጣም ጥሩ የሚባል ነው ወደፊት ደግሞ በንባብ በማዳበር ግንዛቤን በማሳደግ የተሻለ ለመስራት ያስችላችኋል ብለዋል።

ሥልጠናውን የተከታተሉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ደሴ ጥላሁን ይህን መሠል ስትራቴጂክ ሙያዊ አጋርነት መጠናከር ያለበት መሆኑን ጠቁመው ኢንስቲትዩቱ በጥናትና ምርምር ዘርፍ እየሰራ ያለውን የሪፎርም ሥራ የሚያግዝ እና የጥናትና ምርምር አቅማችን የሚሻሽል ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ዕለት መልዕክት ያስተላለፉት የኢንስቲትዩቱ የስልጠናና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አበራ በበኩላቸው ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ከስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመርነውን አጋርነት አጠናክረን እንሠራለን ብለዋል፡፡

ለፍትህና የህግ የልህቀት ማዕከልነት እንተጋለን!

የአብክመ የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

ጥቅምት/2018 ዓ.ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top