


የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት እንደገና ከተደራጀ በኋላ በተሰሩ ስራዎችና በቀጣይ የጋራ ድጋፍ በሚጠይቁ አጀንዳዎች ላይ ከክልሉ ምክር ቤት ጋር ምክክር አደረገ።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 299/2017 ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ተጠሪ ሆኖ እና አዳዲስ ኃላፊነቶች ተሰጠዉት እንደገና ከተቋቋመ በኋላ ፣ በክልሉ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች የልህቀት ማዕከል በመሆን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያለዉ ተቋም ሆኖ እንዲገነባ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን እና ለዚህ የሚሆን ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ፣ የዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቱን አቅም ለመገንባትና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማላቅ እንዲሁም የተቋም መሰረተ-ልማት ሥራዎችን ለማዘመን የሚያስችል ፈንድ ለማፈላለግ የሚያስችል የ5 ዓመት ፕሮጀክት መቀረፁን፤ የኢንስቲትዩቱን ቦታ ለማስፋት ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የቀረበው ጥያቄ ምላሽ ማግነቱን እና 5 ሄክታር ማስፋፊያ መወሰኑን፤ እና የልህቀት ዲዛይን ሥራዎች እና ማማከር ኮርፖሬሽን የሚሰራቸው የህንጻ ግንባታ ዲዛይን ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን እና የዲዛይን ስራው በ3ዲ ምስል በማስደገፍ በማሳየት ፕሮጀክቱ ወደ ስራ እንዲገባ ፕሮጀክቶቹ በበጀት እንዲደገፉ ለማስቻል የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ፤ ምክትል አፈ-ጉባኤ አማረ ሰጤን ጨምሮ ሌሎች የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፤ አማካሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ገለጻ አድርገዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ተቋሙ ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን እና የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች፤ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እና የተለያዩ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ተደራሽ ለማድረግ የዌብሳይት ማልማት ስራ በክልሉ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ማስለማቱን በመግለፅ የቢሮው አመራሮች በተገኙበት ዌብ ሳይቱን ያለሙት ባለሙያዎች ገለፃ እንዲያደርጉ ተደርጓል፤ የዌብሳይቱ አድራሻም በዕለቱ ይፋ የሆነ ሲሆን አድራሻውን፤ https://www.anrsjli.gov.egt ላይ መጎብኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ የለማው ዌብሳይት በኢኖቬሽን ቴክኖሎጅ ከፍተኛ ባለሙያዎች ቀርቦ ደረጃውን የጠበቀና አለማቀፋዊ የመረጃ ትስስር ለመፍጠርና የክልሉ ቀዳሚ የመረጃ ማእከል ለመሆን የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል።
በቀረቡ መነሻ ሰነዶች ላይ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሰፊ ዉይይት ካደረጉ በኋላ ኢንስቲትዩቱ የተሰጠዉን ተልዕኮ በሚመጥን እና ተግባርና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አዲስ ሕንጻ ለመገንባት በተያዘዉ ዕቅድ መሰረት የዲዛይን፣ የቦታ ዝግጅት እና የበጀት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እና ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉ ሊበረታታ የሚገባ ተግባር ነው። የወደፊት ጠቀሜታው ለተቋሙ ብቻ ሳይሆን የክልሉ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ማገልገል የሚያስችል አቅም በመሆኑ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ የሚታሰብበትና የሚከናወን ተግባር መሆኑን አስተያየት የሰጡ ተሳታፊዎች ገልጸው ውይይቱ ተጠናቋል።
