የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት በባህር ዳር ከተማ ለሚያስገነባቸው የህንፃና የፋሲሊቲ ስራዎች በልህቀት ዲዛይንና ማማከር ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተሰራውን የመጀመሪያ ድራፍት ዲዛይን ገመገመ
የአብክመ የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት በአዲስ መልክ በክልሉ ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 299/2017 እንደገና ከተቋቋመ ወዲህ በህጉ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት በመፈፀም የፍትህና የህግ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያግዙትን የተቋም ግንባታ ስራዎች በትኩረት እየሠራ ሲሆን የህንፃና የተለያዩ የፋሲሊቲ አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎች ዲዛይን በልህቀት ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አርክቴክቶችና መሃንዲሶች ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በመድረኩ የልህቀት ዲዛይንና ማማከር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብርሃም አያሌውን ጨምሮ፤ ምክትል ስራ አስፈፃሚው ኢንጂኔር ዘላለም እንየው፤ የኢንስቲትዩታችን ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር)፤ አቶ ሙሉጌታ አበራ (ምክትል ዋና ዳይሬክተር)፤ እና የኢንስቲትዩታችን የስራ አመራር አባላት ተገኝተዋል፡፡
በልህቀት ዲዛይን ኮርፖሬሽን ተሰርቶ የቀረበው የኢንስቲትዩቱ ህንፃዎችና የፋሲሊቲ አገልግሎቶች ዲዛይን በመነሻነት በቀረበው የዲዛይን ኮንሴፕት መሰረት እና ዘርፉ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ በሚመጥን አግባብ የተሰራ ከመሆኑም በላይ ልህቀት ዲዛይን ኮርፖሬሽን የሚገኝበትን ከፍተኛ የባለሙያ አቅም እና የላቀ የመፈፀም ደረጃ ያሳየ መሆኑን ማየት ተችሏል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብርሃም አያሌው የዲዛይን ስራው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተከናወነ መሆኑን እና ከውይይቱም ጠቃሚ ግብዓቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው ኢንስቲትዩቱ ደረጃውን በጠበቀ እና ተወዳዳሪ መሆን በሚችልበት ልክ ሠርተው በማስረከብ የታሪክ አሻራቸውን ማስቀመጥ እንደሚፈልጉም አስረድተዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂኔር ዘላለም እንየው በበኩላቸው ተግባራት የሚጀመሩት ከሃሳብ አመንጭው ነው፤ይህንን ሃሳብ ያመነጩትንም ሆነ ለተግባራዊነቱ በፍጥነትና በተነሳሽነት ወደ ስራ ለገቡት የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበው ፣ የእነሱ ትልቅ ትጋትና ተከሳሽነት ባለሙያውም እነሱን በመከተል ስራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚህ ደረጃ ሊደደርሰው ችሏል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ስራው በተጀመረው ተነሳሽነት እንዲቀጥል ተጨማሪ ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) የልህቀት ዲዛይን ኮርፖሬሽን የዲዛይንና ማማከር ሥራዎች ኮርፖሬሽን በክልል እና በሀገር ደረጃ ከሚሰራቸው የዲዛይንና ማማከር ስራዎች በተጨማሪ ለኢንስቲትዩታችን ስራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በአጭር ጊዜ የዲዛይን ስራው እንዲጠናቀቅ ለተሰጠው አመራር እና የባለሙያዎች ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም ዲዛይኑ ተጠናቆ ወደ ግንባታ ስራ ሲገባ የኮርፖሬሽኑ የማማከር ስራ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው ዲዛይኑ እንዲዳብር የተሰጡ አስተያየቶች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በትኩረት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የህንፃና ፋሲሊቲ ግንባታ ስራዎች ተቋሙ አሁን ላይ ያለበትን የመሰረተ-ልማትና የፋሲሊቲ ማነቆዎች በመሻገር በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለተቋም ግንባታ መሰረት ለመጣል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገለፀዋል፡፡
