- የክልሉ የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት የሥራ ማስጀመሪያና የትውውቅ መድረክ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ኘሬዝዳንትና የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዓለምአንተ አግደው እንዳሉት የክልሉ የፍትሕ ሥርዓት ገለልተኝነቱን ጠብቆ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል። ለዚህም በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ከማድረግ ባሻገር የሕግ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑን ገልፀዋል። ኢንስቲትዩቱ እንደገና መደራጀቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በምርምር ታግዞ ለማስተካከል እንደሚያስችልም ገልጸዋል። ለውጤታማነቱ የዳኞችን፣ የዐቃብያነ-ሕግን፣ የመርማሪ ፖሊሶችንና የሌሎችን አቅም ከማጎልበት ባለፈ በምርምር ዘርፉ ለኢንስቲትዩቱ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነትን በሚያጠናክር አግባብና ሌሎች አዳዲስ ተልዕኮዎችን በመያዝ መልሶ የተደራጀ ነው ብለዋል። ለዚህም በዘርፉ ብቃት ያለው ዳኛ፣ ዐቃቤ-ሕግና ፖሊስ በመገንባት በአገልግሎቱ የፍትሕ ፈላጊውን ማህበረሰብ መተማመን መፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለዚህም የሕግ ማዕቀፎች ያለባቸውን ክፍተት በጥናትና ምርምር በመለየት ማሻሻያዎች ይደረጋሉ ብለዋል። እንዲሁም ማህበረሰቡ የሚጠቀምባቸው አካባቢያዊ ሕጎች የፍትሕ ስርዓቱን እንዲያግዙ ከማድረግ ባሻገር ኢንስቲትዩቱ የሌሎች ሀገራት ልምዶችን በመቀመር የክልሉ የመረጃ ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ይደረጋል ሲሉ አክለዋል።
በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሃናን አበበ በበኩላቸው የፍትሕ ሥርዓቱን ትራንስፎርም የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግርዋል። ለዚህም አገልግሎቶችን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓትና ሌሎች አስር የሚሆኑ የሕግ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ተይዘው እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል። ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ አጋር አካላት ተካተው እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመድረኩ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍትሕ ቢሮ፣ ከፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከሌሎች የዘርፉ ተቋማት የተውጣጡ አመራር አካላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
