በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የተመራ የክልሉ የፍትሕ እና ሕግ ኢንስትቲዩት የበላይ አመራር እና የቦርድ አባላት በፌደራል ፍትሕ እና ሕግ ኢንስትቲዩት እንዲሁም በኦሮሚያ የፍትሕ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ጉብኝት አደረጉ፡፡
በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት፣ 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ የፀደቀ ሲሆን ሕጉም ኢንስቲትዩቱን ገለልተኛ እና ጠንካራ የሆነ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል የሚረዳ ሲሆን የኢንስቲዩቱ ተጠሪነት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲሆን እና የተለያዩ የአደረጃጀት እና የአሰራር ስርዓቶችን ዘርግቷል፡፡
ኢንስቲትዩትም እንደ አዲስ በተቋቋመበት አግባብ የቦርዱ ሠብሳቢ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ አለምአንተ አግደው፣ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር)፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አበራ እና በአዲስ የተዋቀረው የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በፌደራል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስትቲዩት እና የኦሮሚያ የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛን ጎብኝተዋል፡፡
የተደረገው ጉብኝት እና ውይይቱ ከሁለቱም ተቋማት የበላይ አመራሮች ጋር ስለየተቋማቱ የአሰራር ሥርዓት፣ መልካም ተሞክሮዎች፣ የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዲሁም በጋራ የሚሰሩባቸው ጉዳዩች ብሎም እንደ ሀገር ተናባቢ እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከሩ ሲሆን፣ ይህም የአማራ ክልል የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት የያዛቸውን ዘርፈ ብዙ ኃላፊነቶች እና የለውጥ ጉዞ በተሻለ ተግባራዊ ለማድረግ መልካም ልምድ የሚሆን እና ለወደፊት በጋራ ለሚሰሩ ሥራዎችም መሰረት የጣለ ነው፡፡
