
የአማራ ክልል የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ቦርድ 2ኛ መደበኛ ስብሰባዉን በማካሄድ የተለያዩ ዉሳኔዎችን አስተላለፈ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ቦርድ ሃሙስ ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ.ም 2ኛ መደበኛ ስብሰባዉን በማከናወን በመጀመሪያዉ መደበኛ ጉባኤ የተላለፉ ዉሳኔዎችና አቅጣጫዎችን አፈጻጸም ከገመገመ በኋዋላ ፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመያየት ዉሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር አቶ ዓለምአንተ አግደዉ እንደገለፁት ፣ የአማራ ክልል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 299/2017 ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ተጠሪ ሆኖ እና አዳዲስ ኃላፊነቶች ተሰጠዉት እንደገና ከተቋቋመ በኋላ ፣ በክልሉ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች የልህቀት ማዕከል ሆኖ እና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያለዉ ተቋም ሆኖ እንዲገነባ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ እና ለዚህ የሚሆን ስትራቴጅ ወይም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ፤ እስከ አሁን የተሰሩ ሥራዎችም አበረታች መሆናቸዉን ጠቅሰዉ ፣ ቦርዱ የሚያስተላልፋቸዉ ስትራቴጂክ ዉሳኔዎችና የሚሰጠዉ ድጋፍ ይህንን ተሳቢ ያደረገ መሆን እንዳበት ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ ለቦርድ የቀረቡ መነሻ ሰነዶች ላይ የኢንስቲዩቱ ዋና ዳይሬክተርና የቦርዱ ፀሐፊ ዶ/ር ደሴ ጥላሁን ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን ፣ የቦርዱ አባላት ጥያቄዎች ካነሱና አስተያየቶችን ከሰጡ በኋላ ሰፊ ዉይይት ተደርጎ ቦርዱ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ዉሳኔዎችና አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
የኢንስቲትዩትን የ2017 በጀት ዓመት የ12 ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ኢንስቲትዩቱ እንደገና ከተቋቋመ አንድ አመት ጊዜ ዉስጥ የተሰሩ ሥራዎች ዉጤታማ እና ተቋሙ በለዉጥ ሂደት ላይ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ጭምር በማየት ሪፖርቱን አፅድቋል፣
የኢንስቲትዩት የ5 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ (2018-2022) ላይ ዉይይት በማድረግ እና ግብዓቶችን በማከል አፅድቋል ፤ በተመሳሳይ የኢንስቲትዩቱን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አጽድቋል፣
ከኢንስቲትዩቱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ የተዘጋጀውን የፕሮጀክት ዕቅድ (“Barefoot Justice Project of the Institute”) በማፅደቅ ተጨማሪ ሃብት የማፈላለግ ሥራዎች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል፣
በኢንስቲትዩቱ እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት የተቋሙ አደረጃጀት መዋቅር ጥናት እንዲጠና በመወሰን ይህንን የሚያከናዉን ኮሚቴ ሰይሟል፣
ኢንስቲትዩቱ የተሰጠዉን ተልዕኮ በሚመጥን እና ተግባርና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አዲስ ሕንጻ ለመገንባት በተያዘዉ ዕቅድ መሰረት የዲዛይን፣ የቦታ ዝግጅት እና የበጀት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እና ወደ ሥራ እንዲገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፣
የቦርዱ የስብሰባ ሥነ-ስርዓት መመሪያ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል ፤
የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣አሰልጣኞች እና ተመራማሪዎች የደረጃ ፣ የዕደገት እና እርከን መሰላል መመሪያ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል፣
የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣አሰልጣኞች እና ተመራማሪዎች የጥቅማጥቅም መመሪያ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል፣
የመካከለኛ ጊዜ የሥራ ላይ ሥልጠና የሰልጣኞች ክፍያና ወጪ አሸፋፈን ረቂቅ የውሳኔ መነሻ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል፣
በተጨማሪም አዲስ የ18ኛ ዙር ሰልጣኝ ዳኛ እና ዐቃቤ ሕግ ምልመላ ግልጽ የምልመላ መስፈርቶች ወጠዉ እንዲሰራ ዉሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።




